3ኛው የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል:- የፎቶግራፍ እና የአጫጭር ፊልም ውድድሮች ተጀመረ

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በየዓመቱ በሚካሄደው የዘንድሮው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ለዕይታ የሚቀርቡ አጫጭር ፊልሞች እና የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን ውድድር እንደተዘጋጀ እና ውድድሩ በኢሰመኮ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት አሳሳቢ ተብለው በተለዩት በሕይወት የመኖር መብት እና በቂ የሆነ መኖሪያ ቤት በማግኘት መብት ላይ የሚያተኩር መሆኑን ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወቃል። ውድድሩ በመስከረም 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ የተጀመረ ሲሆን፣ እስከ ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ለተወዳዳሪዎች ክፍት ሆኖ የሚቆይ ይሆናል።

ይህ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በኢሰመኮ አዘጋጅነት የሚካሄደው የፊልም ፌስቲቫል “ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን” ማየት የሚለውን የኢሰመኮ ራዕይ ለማሳካት ኪነ ጥበብ ያለውን አስተዋጽዖ፣ እንዲሁም በሁለቱ ዘርፎች መካከል ያለውን ትስስር የሚያስታውስ ነው። ይህንን ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለት የኪነ ጥበብ ዘርፎች በማዘጋጀት፣ ፌስቲቫሉ በየዓመቱ ለዕይታ የሚያቀርባቸውን የኪነ ጥበብ ሥራዎች፣ የሚያሳትፋቸውን የኪነ ጥበብ ዘርፎች፣ የዝግጅቱን ጥራት፣ የሚካሄድባቸውን አካባቢዎች እና ቦታዎች፣ ታዳሚዎችን በብዛት እና ለሰብአዊ መብቶች በሚያደርጉት አስተዋጽዖ ብዝኃነት፣ እንዲሁም በሚያካትታቸው የቋንቋዎች እና የማኅበረሰብ ክፍሎች ብዝኃነት እና በመሳሰሉት መስፈርቶች ሁሉ በየጊዜው እድገት በማሳየት በውድድር ለሚሳተፉ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችም ሆነ በሰብአዊ መብቶች ዘርፎች ለሚሠሩ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መድረክ ለማድረግ ያለመ ነው።

በፎቶግራፍ ውድድሩ ጀማሪዎች (አማተር) ወይም ባለሞያዎች መሳተፍ የሚችሉ ሲሆን፣ ትኩረቱን በቂ የሆነ መኖርያ ቤት የማግኘት መብት ላይ ያደረገ ነው። የአጫጭር ፊልም ውድድሩ ደግሞ በሕይወት የመኖር መብት ላይ ትኩረት በማድረግ፣ በአንድ በኩል በተንቀሳቃሽ ስልክ (ሞባይል) የተቀረጸ እና ከ9 ደቂቃዎች ያልበለጠ አጭር ፊልም ዘርፍ ጀማሪዎችንም ባለሞያዎችንም የሚያሳትፍ፣ በሌላ በኩል በተለይ ባለሞያዎች እንዲሳተፉበት የታለመ እና ከ25 ደቂቃዎች ያልበለጠ ዘጋቢም ሆነ ልብ ወለድ ትረካ ፊልም የሚያወዳድር ነው። 

በሁለቱም የኪነ ጥበብ ዘርፎች ለሁሉም ተሳታፊዎች ልዩ ልዩ የዕውቅና እና የሽልማት ዐይነቶች የተዘጋጁ ሲሆን፣ በተጨማሪም በፎቶግራፍ ውድድር በተለይም ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ለሚወጡ እንደየቅደም ተከተላቸው 40 ሺህ፣ 30 ሺህ እና 20 ሺህ ብር፣ ለሞባይል ፊልም ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ አሸናፊዎች 50 ሺህ፣ 40 ሺህ እና 30 ሺህ ብር እንዲሁም፣ ለአጭር ዘጋቢ ወይም ልብወለድ ፊልም ሥራ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ለሚወጡ 150 ሺህ፣ 120 ሺህ እና 100 ሺህ ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል። (ስለ ውድድሩ የተሟላ መረጃ እዚህ ይገኛል)

ውድድሩ ተሳታፊዎች በቂ ስለሆነ የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብት እና በሕይወት የመኖር መብት ትርጉም የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ፣ ሐሳብ የሚሰጡ፣ የመብቱ መከበር ወይም መጣስ በተጨባጭ ምን እንደሚመስል የሚገልጹ እና ለማሰላሰል የሚጋብዙ የኪነ ጥበብ ሥራዎች የሚያቀርቡበት ይሆናል። ለውድድር የሚቀርቡ የኪነ ጥበብ ሥራዎች በሕይወት የመኖር መብት ወይም በቂ የሆነ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚጠበቁ ቢሆንም፣ ልዩ ትኩረት የሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ማለትም ሕፃናትን እና ታዳጊዎችን፣ ሴቶችን፣ አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን እና ስደተኞችን ለሚያካትቱ የገንዘብን ጨምሮ ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ተዘጋጅተዋል።

በሁለቱም ዘርፎች ማንኛውም ግለሰብ መሳተፍ እንዲችል ቀለል ያሉ የቴክኒክ መስፈርቶች የተቀመጡ ሲሆን፣ ውድድሩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን ወይም የስልጠናና ትምህርት ሰጪ ተቋማት፣ እንዲሁም በእነዚህ ተቋማት የሚሠሩ፣ የሚሰለጥኑ፣ የሚማሩ እና የሚያስተምሩ ግለሰቦች እራሳቸውን ወክለው/በግል መሳተፍ ይችላሉ።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በሁለተኛው ዙር ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል መክፈቻ ባደረጉት ንግግር “የኪነ ጥበብ ሥራዎች ወደውስጣችን እንድንመለከት የሚረዱ፣ አንድነት እና ሰብአዊነትን የሚያወሱ፣ እንዲሁም እርስ በእርስ መከባበርንና መዋደድን የሚያስተምሩ፤ በተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫልን የመሳሰሉ መድረኮች የኪነ ጥበብ ሰዎችን ለተሻለ ራዕይ በማነሳሳት እና ለአንድ ዓላማ በማስተባበር ያላቸውን ድርሻ የሚታሰብበትም ፌስቲቫል ጭምር ነው” ማለታቸውን አስታውሰው፤ “ በዚህ ውድድር በተለይም ወጣቶች እና ታዳጊዎች እንዲሁም በኪነ ጥበብ ዘርፍ ባለሞያዎችን ጨምሮ በኪነ ጥበብ ሥራ ለመሰማራት ያቀዱ እና ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን ለማየት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ጥሪያችንን እና ግብዣችንን ተቀብለው እንዲሳተፉ እንጠይቃለን” ብለዋል።


ስለ ፊልም ፊስቲቫሉ እና ውድድሩ ተጨማሪ ዝርዝር እና የተሟላ ማብራሪያ እዚህ ተያይዟል

የፎቶግራፍ እና የአጫጭር ፊልም ውድድሮች የተሳትፎ ቅጽ እና የውድድሩ አጠቃላይ መመሪያዎች እና ደንቦች