ዝግጅቱ የፌስቲቫል ቅርጽ የያዘ እንደመሆኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በሚገኙ ሲኒማዎች ወይም መሰል ስፍራዎች የሚካሄድ ሲሆን፣ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች ባለሞያዎች፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የከፍተኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች የሚገኙበት ነው።
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ የሚካሄደው ይህ ዓመታዊ ፊልም ፌስቲቫል በእ.ኤ.አ. ታኅሣሥ 10 የሚውለውን ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ቀን የሚያስብ ነው። በተለያዩ የፊልም እና የኪነጥበብ ባለሞያዎች እገዛና ትብብር የሚዘጋጀው ይህ ፌስቲቫል፣ በሰዎች የዕለት ተለት ሕይወት ተጽዕኖ በሚያሳድሩ የሰብአዊ መብቶች ዙርያ የሚያጠነጥኑ አጫጭር ወይም ሙሉ (ፊቸር ፊልሞች)፣ ዘገባዎች ወይም ልብወለድ ይዘት ያላቸው ፊልሞች የሚታዩበት፣ ተመልካቾች ፊልሞቹን ካዘጋጁ ባለሞያዎች ጋር ወይም ከተዋንያን ጋር የሚወያዩበት፣ እንዲሁም የኮሚሽኑን የሰብአዊ መብቶች ሥራዎች የሚደግፉ አጋር ድርጅቶች እና ባለሞያዎች የሚሳተፉበት መድረክ ነው። ዝግጅቱ የፌስቲቫል ቅርጽ የያዘ እንደመሆኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በሚገኙ ሲኒማዎች ወይም መሰል ስፍራዎች የሚካሄድ ሲሆን፣ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች ባለሞያዎች፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የከፍተኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች የሚገኙበት ነው። የሰብአዊ መብቶች ቀን ለማሰብ ያለመ እንደመሆኑ ዓመታዊ ፊልም ፌስቲቫሉ የፊልሞቹን ይዘት የዓመቱን የሰብአዊ መብቶች ቀን መሪ ቃል/መሪ ሐሳብ ከወቅታዊ ሀገራዊ ዐውድ ጋር በማጣጣም፣ ተሳታፊዎችን፣ ባለሞያዎችን እና ተመልካቾችን ከመደበኛ የስብሰባ፣ ስልጠና እና መሰል ዝግጅቶች ለየት ባለ መልኩ ስለሰብአዊ መብቶች እንዲወያዩ በመጋበዝ ግንዛቤ ወይም የሰብአዊ መብቶች እይታ የሚሰጥ ነው።
የሰብአዊ መብቶች ሥራ ዘርፈ ብዙ፣ ሁሉንም ሰዎች የሚመለከት፣ በሁሉም የዕለት ከዕለት ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያለው እንደመሆኑ የሁሉንም አካላት ተሳትፎ፣ ድጋፍ እና ትብብር የሚጠይቅ ነው
መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም የሕዝቡን የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤ እና ዕውቀት ማሳደግ
የኪነ ጥበብ ሰዎችን ለተሻለ ራዕይ ማነሳሳት እና ለአንድ ዓላማ ማስተባበር
የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ከኪነ ጥበብ ዘርፉ ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ማስቻል
የጥበብ ሥራዎች ወደ ውስጣችን እንድንመለከት የሚረዱ፣ አንድነት እና ሰብአዊነትን የሚያወሱ፣ እንዲሁም እርስ በእርስ መከባበርንና መዋደድን የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል የመሳሰሉ መድረኮች የኪነ ጥበብ ሰዎችን ለተሻለ ራዕይ በማነሳሳት እና ለአንድ ዓላማ በማስተባበር ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው
የመጀመሪያው ዙር በአዳማ፣ በአዲስ አበባ እና በሃዋሳ ከተሞች በፊልም እና በሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፍ ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች እና ተማሪዎችን ጨምሮ በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል
ሁለተኛው ዙር በአዳማ፣ በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር፣ በሃዋሳ እና በጅግጅጋ ከተሞች ተካሂዷል። በሁለቱ ዙሮች በአጠቃላይ ከ15 ያላነሱ እና በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ አጫጭር እና ፊቸር ፊልሞች፣ ዘገባዎችና የተለያዩ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ልብወለድ ታሪኮች እና ፊልሞች ታይተዋል። 20 የሚሆኑ የፊልም አዘጋጆችና ባለሞያዎች ሥራዎቻቸውን ለመድረክ አቅርበውበታል፣ እንዲሁም ከ10 ያላነሱ የኮሚሽኑ አጋር ተቋማት ተሳትፈውበታል።
በሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫሉ የሚሳተፉ የኪነ ጥበብ ዘርፎችን በማስፋት፣ በመድረኩ የሚታዩ ፊልሞችንና ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ይዘት ጥራት ለማሳደግ የሚረዱ ውድድሮችና መሰል አሳታፊ ዝግጅቶችን በማካሄድ፣ የሚሳተፉ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችን ቁጥር በመጨመር እና ዝግጅቶቹ የሚካሄዱባቸውን ከተሞች ቁጥር በማብዛት የፌስቲቫሉን ይዘት እና አካታችነት ማስፋት ተችሏል።
በ2017 ፌስቲቫሉ በአዳዲስ ከተሞች፣ በአዳዲስ ዝግጅቶች እና በአዳዲስ ውድድሮች መጥቷል።
ኢሰመኮ በፊልም ፌስቲቫሉ ለዕይታ የሚቀርቡ የሴቶች ሕይወት እና በቂ ምግብና ውሃ የማግኘት መብት ላይ ትኩረት በማድረግ ውድድሮች አዘጋጅቷል
ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫሎች ሰዎችን በአንድ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ ዙርያ የማሰባሰብና የማስተባበር ጠቀሜታቸው የጎላ የሚሆነው በቅርጻቸው፣ በይዘታቸውና በአጠቃላይ ዝግጅታቸው በየጊዜው የሚሻሻል ሲሆን ነው። ስለሆነም በኢሰመኮ አዘጋጅነት የሚካሄደው ይህ የኪነ ጥበብና የሰብአዊ መብቶች ጥምር መድረክ ለዝግጅቱ መሳካት አዳዲስ ሐሳብ በማቅረብ፣ የተለያዩ ዓይነት ድጋፎችን በማድረግ፣ በማስተዋወቅ፣ ፊልሞቻቸውን በመድረኩ እንዲታዩ ፈቃድ በመስጠት ወይም በተለያዩ የዝግጅቱ ሂደቶች በአስተባባሪነትም ሆነ በሌላ መንገድ በመተባበር የሚሳተፉ ድርጅቶች ጋር ይተባበራል። በተለያዩ ሀገራዊ ቋንቋዎችና በልዩ ልዩ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ዙርያ የተሠሩ ጥራት ያላቸው ፊልሞችን ያፈላልጋል እንዲሁም እነዚህን የተመረጡ ፊልሞች ተደራሽነት ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት ይቀጥላል። በሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫሉ የሚሳተፉ የኪነ ጥበብ ዘርፎችን ከዓመት ዓመት በማስፋት፣ በመድረኩ የሚታዩ ፊልሞችና ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ይዘት ጥራት ለማሳደግ የሚረዱ ውድድሮችና መሰል አሳታፊ ዝግጅቶችን በማካሄድ፣ የሚሳተፉ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችን ቁጥር በመጨመር፣ ዝግጅቶቹ የሚካሄዱባቸውን ከተሞች ቁጥር በማብዛት ኢሰመኮ የፊልም ፌስቲቫሉን እድገትና ዓላማ ለማሳካት ይሠራል።
This site was created with the Nicepage