በመርኃ ግብሩ የሚቀርቡ ፎቶግራፎች፣ ሥዕል፣ አጫጭር ፊልሞች እና አጫጭር የሥነ ጽሑፍ ውድድር : በ2017 ዓ.ም. በታኅሣሥ 01 ቀን የሚውለው ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ቀን (December 10) በማስመልከት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ4ኛው ዙር የፊልም ፌስቲቫል ለዕይታ የሚቀርቡ የፎቶግራፍ፣ የአጫጭር ቪዲዮዎች እና የአጫጭር ሥነ ጽሑፍ ውድድሮች ያዘጋጀ ሲሆን፣ በውድድሩ ለመሳተፍ እና ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ዝርዝሩን ይመልከቱ
የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን ለማሰብ የተዘጋጀው አራተኛው የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ዓመታዊ ፊልም ፌስቲቫል በኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን፣ በዝግጅቱ ለዕይታ ከሚቀርቡ የፊልም ውጤቶች በተጨማሪ የተለያዩ የኪነጥበብ ሥራዎች ማለትም የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን፣ ሥዕል እና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ይገኙበታል። በዚህ ፌስቲቫል በተለያዩ ከተሞች በሚዘጋጁ መርኃ ግብሮች ላይ ለዕይታ የሚቀርቡ ፎቶግራፎች፣ የሥዕል ሥራዎችና ሥነ ጽሑፎች የተለያዩ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች በሚሳተፉበት ውድድር ከዝግጅቱ ቀን አስቀድሞ የሚመረጡ ናቸው።
ጭብጥ፡- በቂ ምግብ እና ውሃ የማግኘት መብት
ጭብጥ፡- የሴቶች ሕይወት እና በቂ ምግብ እና ውሃ የማግኘት መብት
የፎቶግራፍ ውድድር
ይህ የውድድር ዘርፍ ምግብና ውሃ በማግኘት መብት ላይ የሚያተኩር ሲሆን ተሳታፊዎች በቂ ስለሆነ ምግብና ውሃ የማግኘት መብት የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ፣ ሐሳብ የሚሰጡ፣ የመብቱ መከበር ወይም መጣስ በተጨባጭ ምን እንደሚመስል የሚገልጹ እና ለማሰላሰል የሚጋብዙ ምስሎችን (ፎቶግራፎችን) የሚያቀርቡበት ነው።
በቂ የሆነ ምግብ እና ውሃ ማለት ምን ማለት ነው? ምግብ እና ውሃ የሌለው ሰው አኗኗር ምን ይመስላል? ምግብና ውሃ የማግኘት መብት ለሴቶች እና ለወንዶች አንድ ዐይነት ትርጉም አለው? የአካል ጉዳተኞች ምግብና ውሃ የማግኘት መብት ምን ይመስላል?
ይህ የፎቶግራፍ ውድድር ዘርፍ እነዚህን እና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በምስል ለመግለጽ እና ለማሰላሰል የሚጋብዝ ነው። በዚህ የውድድር ዘርፍ በጀማሪም ይሁን ልምድ ባለው ባለሙያ ለሚቀርቡ የኪነጥበብ ሥራዎች የመወዳደሪያ መስፈርቶች ተመሳሳይ ናቸው።
የአጫጭር ሥነ ጽሁፎች ውድድር
ይህ የውድድር ዘርፍ በሕይወት የመኖር መብት በተለይም በሴቶች ሕይወት እና በቂ ምግብና ውሃ ማግኘት ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ተሳታፊዎች ስለ ሴቶች ሕይወት እንዲሁም በቂ ምግብና ውሃ የማግኘት መብት ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ፣ ሐሳብ የሚሰጡ፣ የመብቱ መከበር ወይም መጣስ በተጨባጭ ምን እንደሚመስል የሚገልጹ እና ለማሰላሰል የሚጋብዙ አጫጭር የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን የሚያቀርቡበት ነው።
ይህ የአጫጭር ሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ውድድር ዘርፍ የሚሸፍነው ርዕሰ ጉዳዩ ሰፊ እንደመሆኑ መጠን የሥነ ጽሑፍ ውጤቱ በግጥም ወይም በስድ ንባብ/ ጽሑፍ መልክ ሊቀርብ ይችላል። በዚህ የውድድር ዘርፍ ልብ ወለድ አልያም በእውነተኛ ታሪክ ላይ መሠረት ያደረጉ ታሪኮችን/ ክስተቶችን ማቅረብ የሚቻል ይሆናል። እንደ ሌሎቹ የውድድር ዘርፎች ሁሉ በዚህ ውድድር መመሪያ እና ደንቦች በተገለጸው መሠረት ማስታወቂያ የሚያካትቱ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ከውድድሩ ውጪ ይደረጋሉ።
በዚህ ዘርፍ በጀማሪም ይሁን ልምድ ባለው የሥነ ጽሑፍ ባለሙያ የተዘጋጁ እና ለውድድር የሚቀርቡ አጫጭር የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች የመወዳደሪያ መስፈርቶች ልዩነት የላቸውም።
ለውድድር የሚቀርበው ፎቶግራፍ ለዘርፉ ከተመደበው ጭብጥ/ ርዕሰ ጉዳይ ጋር (በቂ ምግብና ውሃ የማግኘት መብት) ተያያዥነት ያለው ሊሆን ይገባል።
በዚህ ዘርፍ የሚቀርቡ የፎቶግራፍ/ የኪነጥበብ ሥራዎች ከመስከረም ወር 2016 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ የተነሱ/የተወሰዱ ሊሆኑ ይገባል።
ለዚህ ውድድር የሚቀርቡ የኪነጥበብ ሥራዎች ከ1 ሜጋ ባይት ያላነሱ እና ከ5 ሜጋ ባይት ያልበለጡ ሊሆኑ ይገባል።
በ JPEG ሴቭ የተደረጉ እና በተቻለ መጠን ለኅትመት አመቺ በሆነ ከፍተኛ የጥራት (ሪዞሉሽን) ደረጃ ሊሆኑ ይገባል።
ለፎቶግራፍ ሥራ ከሚያስፈልገው የአርትዖት (editing) ሥራ በተጨማሪ፣ መጠነኛ በሆነ መልኩ ፎቶግራፉን ለማሳመር የሚደረጉ (digital manipulations) ሥራዎች ተቀባይነት አላቸው። ሆኖም እነኚህ ለውጦች ምን እንደሆኑ እና ለምን ዓላማ እንደተሠሩ በተሳትፎ ቅጹ ላይ በግልጽ ሊመላከት ይገባል። የውድድሩ አዘጋጆች ይህንን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለተሳታፊው ሊያቀርቡ ይችላሉ። እንዲሁም ተጨማሪ ሥራዎች ያልተሠራበትን (ኦሪጂናል) ፎቶግራፍ እንዲላክ ሊጠይቁ ይችላሉ።
ተሳታፊው የሚጠቀመው ካሜራ ቢያንስ 3000 ፒክሰል (ወደ ጎን) እና 300 DPI/PPI setting ሊሆን ይገባል። በሞባይል/ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚነሱ ፎቶግራፎች ይህንን መስፈርት ማሟላት የሚጠበቅባቸው ባይሆንም፣ ለውድድር ተቀባይነት የሚኖራቸው ከፍተኛ ጥራት (high resolution) ያላቸው እና ከተመደበው ጭብጥ/ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ከሆነ ብቻ ነው።
በተለይ በአንድ ሰው ላይ የሚያተኩሩ ፎቶግራፎች ከሆኑ የዛን ሰው ሙሉ ፈቃድ ማግኘት፣ ከ18 ዓመት በታች ከሆኑ ደግሞ በሕግ ሙሉ መብት ያለውን ወይም የአሳዳጊ ሙሉ ፈቃድ ማግኘትዎን ያረጋግጡ።
Collage ወይም በአንድ ፍሬም በርካታ ምስሎችን የያዘ ፎቶግራፍ በውድድሩ አይካተትም። ለውድድር በሚቀርበው ፎቶግራፍ ላይ ፊርማ፣ watermark፣ overlay እና የመሳሰሉትን ምልክቶች ወይም ጽሑፎች መጨመር አይገባም።
አጫጭር ሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ግጥም ወይም ዝርው ጽሑፍ ሊሆኑ ይችላሉ።
ለውድድር ዘርፉ ከተመደበው ጭብጥ/ ርዕሰ ጉዳይ (በሕይወት የመኖር መብት (የሴቶች ሕይወት) እና ከበቂ የምግብና የውሃ መብት) ጋር የተያያዘ መሆን አለበት።
የአጭር ሥነ ጽሑፉ ርዝመት ከሁለት ገጽ ያላነስ እና ከአራት ገጽ ያልበለጠ ወይም ከ600 ቃላት ያላነስ እና ከ1200 ቃላት ያልበለጠ ሊሆን ይገባል።
በዚህ ዘርፍ የሚቀርቡ ሥራዎች ከመስከረም ወር 2016 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ የተጻፉ ሊሆኑ ይገባል።
በማንኛውም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተጻፈ አጭር ጽሑፍ ለውድድሩ መቅረብ ይችላል። ሆኖም ጽሑፉ በአማርኛ ወይም በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተተርጉሞ አባሪ ሆኖ ሊቀርብ ይገባል።
ጽሑፉ በMS word ተጽፎ መቅረብ ያለበት ሲሆን ርዕሱ በ14 ይዘቱ ደግሞ በ 12 font size እና በነጠላ መስመር ክፍተት (single line spacing) መሆን አለበት።
ከሰብአዊ መብቶች እና ከዘንድሮ ጭብጦች ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ፊልሞች ይታያሉ
በሴቶች ሕይወት እና በበቂ ምግብና ውሃ የማግኘት መብት ዙርያ በተሠሩ የኪነጥበብ ሥራዎች መካከል በሚደረግ ውድድር የተለዩ አሸናፊዎች ይሸለማሉ
በባለሙያዎች እና በታዳሚዎች መካከል ውይይት ይካሄዳል
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች እንዲገናኙ የሚያስችል መድረክ
ሰንሻይን ታወር ቁጥር 5፣ መስቀል አደባባይ አለፍ ብሎ ቦሌ መንገድ፣ ሀያት ሬጀንሲ ሆቴል አጠገብ፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
This site was created with the Nicepage