የዘንድሮ ውድድር ጭብጥ፡- የሴቶች ሕይወት እና በቂ ምግብ እና ውሃ የማግኘት መብት
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት ለ4ኛ ጊዜ የሚካሄደው የሰብአዊ መብቶች ዓመታዊ ፊልም ፌስቲቫል በኢሰመኮ የ2016 በጀት ዓመት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ በመሆን ከተለዩት ጉዳዮች መካከል በሴቶች ሕይወት (በሕይወት የመኖር መብት) እና በቂ ምግብና ውሃ የማግኘት መብቶች ዙሪያ የሚያተኩር ነው፡፡ በሕይወት የመኖር መብት በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ተብለው ከሚመደቡት መብቶች አንዱ ሲሆን፣ በሕይወት የመኖር መብት ስለሚያካትታቸው ጉዳዮች እና መብቱ የሚጣስባቸውን ሁኔታዎች በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ እዚህ ተያይዟል። ማንኛውም ሰው በቂ ምግብና ውሃ የማግኘት መብት ያለው ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች በመባል ከተለዩት መብቶች መካከል አንዱ ነው። መብቱ በቂ ምግብ የማግኘት መብት ሰፊና በርካታ ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች የሚዳስስ መብት ነው። ይህንን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ እዚህ ተያይዟል። የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን ለማሰብ የተዘጋጀው አራተኛው የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ዓመታዊ ፊልም ፌስቲቫል በኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን፣ በዝግጅቱ ለዕይታ ከሚቀርቡ የፊልም ውጤቶች በተጨማሪ የተለያዩ የኪነጥበብ ሥራዎች ማለትም የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን፣ ሥዕል እና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ይገኙበታል። በዚህ ፌስቲቫል በተለያዩ ከተሞች በሚዘጋጁ መርኃ ግብሮች ላይ ለዕይታ የሚቀርቡ ፎቶግራፎች፣ የሥዕል ሥራዎችና ሥነ ጽሑፎች የተለያዩ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች በሚሳተፉበት ውድድር ከዝግጅቱ ቀን አስቀድሞ የሚመረጡ ናቸው።
የውድድር ጊዜው ጥቅምት 01 ቀን 2017 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. እኩለ ለሊት (በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከለሊቱ 6፡00 ሰዓት) ድረስ ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች በእነዚህ ቀናት ለውድድር የሚያቀርቧቸውን የኪነጥበብ ሥራዎች ከሥር በተመለከተው አድራሻ፣ እዚህ የተያያዘውን ቅጽ በመሙላት መላክ ይችላሉ። ለውድድር የተላኩ የኪነጥበብ ሥራዎች በሁለት ዙር የሚገመገሙ ይሆናል። በመጀመሪያው ዙር፡ በኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሚውለው የኢሰመኮ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ዝግጅት ለዕይታ የሚቀርቡ የኪነጥበብ ሥራዎች ይመረጣሉ፣ በሁለተኛው ዙር፡ በኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሚውለው ዝግጅት በየከተማው ለዕይታ እንዲቀርቡ ከተመረጡ ሥራዎች መካከል ከአንደኛ እስከ አስረኛ ደረጃ የወጣላቸው የኪነጥበብ ሥራዎች እጩ የሚደረጉበት ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ የሚመደቡ የኪነጥበብ ሥራዎች ይመረጣሉ። ከአንደኛ እስከ አስረኛ የወጡ እንዲሁም ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የተመደቡ የኪነጥበብ ሥራዎች ውድድሩ በተካሄደባቸው ከተሞች በሚዘጋጀው የመክፈቻ ዝግጅት ላይ የሚገለጹ ሲሆን፣ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የተመደቡ የኪነጥበብ ሥራዎች እያንዳንዳቸው በመድረኩ ላይ በመቅረብ ይሸለማሉ። ለሁሉም የኪነጥበባ ሥራዎች ውድድር ተሳታፊዎች የተሳትፎ ዕውቅና ሰርተፊኬት ይሰጣል። እንዲሁም ተጨማሪ ተያያዥ ማበረታቻዎች እንደ አግባብነቱ ለተሳታፊዎች ይገለጻል። ሆኖም ከኢሰመኮ እሴቶች እና መርሖች አንዱ ግልጽነት በመሆኑ በየከተማው በውድድሩ የተሳተፉ ግለሰቦች እና ተቋማት፣ እንዲሁም የቀረቡት የኪነጥበብ ሥራዎች በሙሉ በኢሰመኮ ድረገጽ እና ማኅበራዊ ትስስር ገጾች እንዲሁም በተለያዩ አመቺ መንገዶች የሚገለጹ ይሆናሉ።
የዓመታዊው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ዋነኛ ዓላማ የኪነጥበብን እና የሰብአዊ መብቶችን ትስስር ለማጠናከር እና በሁለቱ ዘርፎች መካከል ያለውን ጥምረት በተመለከተ ግንዛቤ ለማስፋፋት፣ እንዲሁም ኪነጥበብ “ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን ማየት” የሚለው የኢሰመኮ ራዕይ መሳካት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለማስታወስ ነው። በተጨማሪም የፊልም ፌስቲቫሉ የኪነጥበብ ሥራዎችን በውድድር መልኩ ሲጋብዝ ይህ ሁለተኛው ጊዜ ሲሆን፣ የዚህ ዙር ዓላማ በርካታ ተወዳዳሪዎችን መጋበዝ እና እንዲሳተፉ ማበረታታት ነው። በመሆኑም ለውድድሩ የሚቀርቡ ሥራዎች የቴክኒክ መስፈርቶች ቀለል ያሉ እና በአብዛኛው በተለይም ትኩረት ከተደረገባቸው በሴቶች ሕይወት (በሕይወት የመኖር መብት) እና በቂ የሆነ ምግብና ውሃ የማግኘት መብት ጋር ባላቸው ተያያዥነት የሚገመገሙ ይሆናሉ። ለዚህ ሂደት የጥበብ ሥራዎቹን የቴክኒክ መስፈርት የሚገመግም አንድ ባለሞያ፣ ከሦስተኛው ዙር አሸናፊዎች፣ በተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ዘርፎች (በሲቪል እና ፖለቲካ፣ በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ፣ በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞች፣ በአረጋውያን፣ እንዲሁም በስደተኞች፣ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና በፍልሰተኞች መብቶች) የሚሠሩ የኢሰመኮ እና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሙያዎች፣ የኢሰመኮ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራ ክፍል ባለሙያዎች እና ሌሎች አግባብነት ያላቸው የሥራ ክፍሎች ባለሙያዎች የተካተቱበት፣ ለመጀመሪያ ዙር ግምገማ የ5 ገምጋሚዎች ፓነል፣ ለሁለተኛ ዙር ግምገማ የ7 ገምጋሚዎች ፓነል ይቋቋማሉ። ገምጋሚዎች ከዚህ በታች በተዘረዘሩት የማወዳደሪያ መስፈርቶች ለኪነጥበብ ሥራዎቹ ነጥብ የሚሰጡ ሲሆን፣ ሁሉም ገምጋሚዎች የሰጡት ነጥቦች ድምር አማካይ የኪነጥበብ ሥራው የመጨረሻ ውጤት ይሆናል። ሁለት የኪነጥበብ ሥራዎች ተመሳሳይ ውጤት በሚያገኙበት ጊዜ በገምጋሚ ፓነሉ አብላጫ ድምጽ የሚወሰን ይሆናል። የገምጋሚ ፓነሉ ውሳኔ የመጨረሻ ነው።
• በሚከተሉት የማኅበረሰብ ክፍሎች (ልዩ ትኩረት የማኅበረሰብ ክፍሎች) ላይ ለሚያተኩሩ ለውድድር የሚቀርቡ ሁሉም የኪነጥበብ ሥራዎች ለውድድሩ መስፈርቶች ከሚሰጡ ነጥቦች በተጨማሪ የማበረታቻ ነጥቦች (bonus) ያገኛሉ፦ – በሕፃናት እና ታዳጊዎች (ዕድሜያቸው ከ18 ያልበለጡ) – በሴቶች – በአረጋውያን – በአካል ጉዳተኞች – በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወይም በስደተኞች • ማንኛውም ግለሰብ፣ ማናቸውም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን ድርጅት፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን ወይም የስልጠናና ትምህርት ሰጪ ተቋማት ወይም በተዘረዘሩት ተቋማት የሚሠሩ፣ የሚሰለጥኑ፣ የሚማሩ እና የሚያስተምሩ ግለሰቦች በሁሉም የውድድር ዘፎች እራሳቸውን ወክለው/በግል መሳተፍ ይችላሉ። • በውድድሩ ለመሳተፍ ኢትዮጵያዊ መሆን ያስፈልጋል። ውድድሩ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን እና ተቋማትን ለማበረታታት እና ዐቅም ለመገንባት ያለመ እንደመሆኑ በሀገር ውስጥ የተመዘገቡ፣አልያም ተቀማጭነታቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉ ቢሆኑም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ለሆኑ የሲቪክ ማኅበረሰብም ሆነ ሌሎች ተቋማት ክፍት አይደለም። • በውድድር ለመሳተፍ ምንም ዐይነት ክፍያ አይጠየቅም። • የኢሰመኮ ሠራተኞች በሁሉም የውድድር ዘርፎች መሳተፍ የሚችሉ ሲሆን፣ የጥበብ ሥራዎቹ ለዕይታ ለመቅረብ ብቁ ሆነው ከተገኙ ሊመረጡ ይችላሉ። ሆኖም በውድድሩ ለሽልማት እጩ ከሚሆኑ የጥበብ ሥራዎች መካከል አይካተቱም። • በአንድ የውድድር ዘርፍ የኪነጥበብ ሥራውን ያቀረበ ተሳታፊ በሌላ ዘርፍ ተጨማሪ የጥበብ ሥራ ለውድድር ማቅረብ አይችልም። ስለሆነም ተሳታፊዎች በአንድ ዘርፍ ብቻ የሚወዳደሩ ይሆናል። • በተጨማሪም አንድ ተሳታፊ በሚወዳደርበት ዘርፍ ከአንድ በላይ የኪነጥበብ ሥራ ማወዳደር አይችልም። • ተሳታፊዎች ለሌሎች ውድድሮች ያቀረቧቸውን የኪነጥበብ ሥራዎች ለዚህ ውድድር ማቅረብ ይችላሉ።• የውድድሩ አዘጋጆች ተጨማሪ ማብራሪያ ወይም መረጃ አልያም ከውድድሩ ጋር በተያያዘ ሌላ ምክንያት ተሳታፊዎችን በተሳትፎ ቅጹ ባስቀመጡት አድራሻ ለማግኘት ሞክረው፣ ተሳታፊዎች በተገለጸው አድራሻ በተገቢው ጊዜ በማይገኙበት ወይም ምላሽ በማይሰጡበት ወቅት የውድድሩ አዘጋጆች ለውድድር የቀረበውን ሥራ ከውድድሩ ውጪ ሊያደርጉ ይችላሉ። ይህም የኢሰመኮ ውሳኔ የመጨረሻ ነው። • ተሳታፊዎች ከሚወክሉት ተቋም ወይም ከእራሳቸው ውጪ ያሉ (የሦስተኛ ወገንን) የኪነጥበብ/ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ለውድድሩ ማቅረብ አይችሉም። የኢሰመኮ ይህንን የማረጋገጥ ሙሉ መብት የተጠበቀ ነው። • በአንድ የውድድር ዘርፍ በብዛት እና በብቁነት በቂ ተወዳዳሪ አለመኖሩ ከድምዳሜ ላይ ከተደረሰ፣ የውድድሩ አዘጋጆች የውድድር ዘርፉን ሊሰርዙ ይችላሉ። ይህም ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል። ሆኖም ኢሰመኮ በተሰረዘው የውድድር ዘርፍ የተላኩ የኪነጥበብ ሥራዎችን ለተሳታፊዎች የመመለስ ግዴታ ያለበት ሲሆን፣ በተሳትፎ መመሪያ እና ደንቦች አንቀጽ (2) እና (8) መሠረት ጥቅም ላይ ማዋል አይችልም።
ይህ የውድድር ዘርፍ በሕይወት የመኖር መብት በተለይም በሴቶች ሕይወት እና በቂ ምግብና ውሃ ማግኘት ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ተሳታፊዎች ስለ ሴቶች ሕይወት እንዲሁም በቂ ምግብና ውሃ የማግኘት መብት ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ፣ ሐሳብ የሚሰጡ፣ የመብቱ መከበር ወይም መጣስ በተጨባጭ ምን እንደሚመስል የሚገልጹ እና ለማሰላሰል የሚጋብዙ አጫጭር የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን የሚያቀርቡበት ነው። ይህ የአጫጭር ሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ውድድር ዘርፍ የሚሸፍነው ርዕሰ ጉዳዩ ሰፊ እንደመሆኑ መጠን የሥነ ጽሑፍ ውጤቱ በግጥም ወይም በስድ ንባብ/ ጽሑፍ መልክ ሊቀርብ ይችላል። በዚህ የውድድር ዘርፍ ልብ ወለድ አልያም በእውነተኛ ታሪክ ላይ መሠረት ያደረጉ ታሪኮችን/ ክስተቶችን ማቅረብ የሚቻል ይሆናል። እንደ ሌሎቹ የውድድር ዘርፎች ሁሉ በዚህ ውድድር መመሪያ እና ደንቦች በተገለጸው መሠረት ማስታወቂያ የሚያካትቱ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ከውድድሩ ውጪ ይደረጋሉ። በዚህ ዘርፍ በጀማሪም ይሁን ልምድ ባለው የሥነ ጽሑፍ ባለሙያ የተዘጋጁ እና ለውድድር የሚቀርቡ አጫጭር የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች የመወዳደሪያ መስፈርቶች ልዩነት የላቸውም።
1. አጫጭር ሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ግጥም ወይም ዝርው ጽሑፍ ሊሆኑ ይችላሉ። 2. ለውድድር ዘርፉ ከተመደበው ጭብጥ/ ርዕሰ ጉዳይ (በሕይወት የመኖር መብት (የሴቶች ሕይወት) እና ከበቂ የምግብና የውሃ መብት) ጋር የተያያዘ መሆን አለበት። 3. የአጭር ሥነ ጽሑፉ ርዝመት ከሁለት ገጽ ያላነስ እና ከአራት ገጽ ያልበለጠ ወይም ከ600 ቃላት ያላነስ እና ከ1200 ቃላት ያልበለጠ ሊሆን ይገባል። 4. በዚህ ዘርፍ የሚቀርቡ ሥራዎች ከመስከረም ወር 2016 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ የተጻፉ ሊሆኑ ይገባል። 5. በማንኛውም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተጻፈ አጭር ጽሑፍ ለውድድሩ መቅረብ ይችላል። ሆኖም ጽሑፉ በአማርኛ ወይም በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተተርጉሞ አባሪ ሆኖ ሊቀርብ ይገባል። 6. ጽሑፉ በMS word ተጽፎ መቅረብ ያለበት ሲሆን ርዕሱ በ14 ይዘቱ ደግሞ በ 12 font size እና በነጠላ መስመር ክፍተት (single line spacing) መሆን አለበት።
ከጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. (እኩለ ለሊት ወይም በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከለሊቱ 6፡00 ሰዓት) ድረስ ለውድድር የሚቀርበውን የኪነ ጥበብ ሥራ እንዲሁም የተሞላ እና የተፈረመበት የተሳትፎ ቅጽ በማያያዝ ከዚህ በታች በተመለከተው አድራሻ መላክ ይችላሉ።
This site was created with the Nicepage