ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫሎች ሰዎችን በአንድ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ ዙርያ የማሰባሰብና የማስተባበር ጠቀሜታቸው የጎላ የሚሆነው በቅርጻቸው፣ በይዘታቸውና በአጠቃላይ ዝግጅታቸው በየጊዜው የሚሻሻል ሲሆን ነው። ስለሆነም በኢሰመኮ አዘጋጅነት የሚካሄደው ይህ የኪነ ጥበብና የሰብአዊ መብቶች ጥምር መድረክ ለዝግጅቱ መሳካት አዳዲስ ሐሳብ በማቅረብ፣ የተለያዩ ዓይነት ድጋፎችን በማድረግ፣ በማስተዋወቅ፣ ፊልሞቻቸውን በመድረኩ እንዲታዩ ፈቃድ በመስጠት ወይም በተለያዩ የዝግጅቱ ሂደቶች በአስተባባሪነትም ሆነ በሌላ መንገድ በመተባበር የሚሳተፉ ድርጅቶች ጋር ይተባበራል። በተለያዩ ሀገራዊ ቋንቋዎችና በልዩ ልዩ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ዙርያ የተሠሩ ጥራት ያላቸው ፊልሞችን ያፈላልጋል እንዲሁም እነዚህን የተመረጡ ፊልሞች ተደራሽነት ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት ይቀጥላል።
በሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫሉ የሚሳተፉ የኪነ ጥበብ ዘርፎችን ከዓመት ዓመት በማስፋት፣ በመድረኩ የሚታዩ ፊልሞችና ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ይዘት ጥራት ለማሳደግ የሚረዱ ውድድሮችና መሰል አሳታፊ ዝግጅቶችን በማካሄድ፣ የሚሳተፉ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችን ቁጥር በመጨመር፣ ዝግጅቶቹ የሚካሄዱባቸውን ከተሞች ቁጥር በማብዛት ኢሰመኮ የፊልም ፌስቲቫሉን እድገትና ዓላማ ለማሳካት ይሠራል።
This site was created with the Nicepage