የዘንድሮ ውድድር ጭብጥ፡- የነጻነት መብት እና የትምህርት መብት
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት ለ5ኛ ጊዜ የሚካሄደው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በኢሰመኮ የ2017 በጀት ዓመት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ በመሆን ከተለዩት ጉዳዮች መካከል በነጻነት መብት እና በትምህርት መብት ዙሪያ የሚያተኩር ይሆናል። የነጻነት መብት በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ተብለው ከሚመደቡት መብቶች አንዱ ሲሆን፣ የነጻነት መብት ስለሚያካትታቸው ጉዳዮች እና መብቱ የሚጣስባቸውን ሁኔታዎች በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ እዚህ ተያይዟል። ማንኛውም ሰው ትምህርት የማግኘት መብት ያለው ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች በመባል ከተለዩት መብቶች መካከል አንዱ ነው። መብቱ ትምህርት የማግኘት መብትን እና ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች የሚዳስስ መብት ነው። ይህንን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ እዚህ ተያይዘዋል። የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን ለማሰብ የሚዘጋጀው አምስተኛው የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ዓመታዊ ፊልም ፌስቲቫል በኅዳር 27/ ታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን፣ በዝግጅቱ ከሚቀርቡ የተለያዩ የኪነጥበብ ሥራዎች መካከል የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን እና አጫጭር ፊልሞች ይገኙበታል። በዚህ ፌስቲቫል በተለያዩ ከተሞች በሚዘጋጁ መርኃ ግብሮች ላይ ለዕይታ የሚቀርቡ ፎቶግራፎች እና አጫጭር ፊልሞች የተለያዩ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች በሚሳተፉበት ውድድር ከዝግጅቱ ቀን አስቀድሞ የሚመረጡ ናቸው። በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚካሄደው ይህ ፌስቲቫል የፎቶግራፎች እና የአጫጭር ፊልሞች ውድድሮችን ያካተተ ሲሆን ተሳታፊዎች በአንድ ወይም ከዛበላይ በሆኑ ዘርፎች ከታች በተዘረዘረው መሠረት በውድድሩ የሚሳተፉ ይሆናል፦ ውድድሩ የሚካሄድባቸው ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች – በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች (አዲሰ አበባ፣ ድሬዳዋ ከተሞች እና አፋር፣ በአማራ፣ ቤንሻንጉል፣ ማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ሶማሊ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ትግራይ ክልሎች) የውድድር ዘርፍ – የፎቶግራፍ ውድድር (የትምህርት መብት ላይ በማተኮር)፣ አጫጭር ፊልም ለጀማሪዎች (5-6 ደቂቃ) እና ለባለሙያዎች (10-15 ደቂቃ) (የነጻነት መብት ላይ በማተኮር)
የውድድር ጊዜው ከመስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2018 ዓ.ም. (እኩለ ለሊት ወይም በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከለሊቱ 6፡00 ሰዓት) ድረስ ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች በእነዚህ ቀናት ለውድድር የሚያቀርቧቸውን ሥራዎች ከሥር በተመለከተው አድራሻ፣ እዚህ ከተያያዘው ቅጽ ጋር መላክ ይችላሉ። ለውድድር የተላኩ የኪነጥበብ ሥራዎች በሁለት ዙር የሚገመገሙ ይሆናሉ። በመጀመሪያ ዙር፡ በኅዳር 27/ ታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሚውለው የኢሰመኮ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ዝግጅት ለዕይታ የሚቀርቡ የኪነጥበብ ሥራዎች ይመረጣሉ፣ በሁለተኛ ዙር፡ በኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሚውለው ዝግጅት በየከተማው ለዕይታ እንዲቀርቡ ከተመረጡ ሥራዎች መካከል ከአንደኛ እስከ አስረኛ ደረጃ የወጣላቸው የኪነጥበብ ሥራዎች እጩ የሚደረጉበት ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ የሚመደቡ የኪነጥበብ ሥራዎች ይመረጣሉ። ከአንደኛ እስከ አስረኛ የወጡ የኪነጥበብ ሥራዎች ሙሉ ዝርዝር፣ እንዲሁም ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የተመደቡ የጥበብ ሥራዎች ፌስቲቫሉ በሚካሄደባቸው ከተሞች እና በመክፈቻ ዝግጅት ላይ በይፋ የሚገለጹ ሲሆን፣ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የተመደቡ የኪነጥበብ ሥራዎች እያንዳንዳቸው በመድረኩ ላይ በመቅረብ ይሸለማሉ። በተጨማሪም ለውድድር የቀረቡ የኪነጥበብ ሥራዎች በሙሉ የተሳትፎ ዕውቅና ሰርተፊኬት ይሰጣል። ሆኖም ከኢሰመኮ እሴቶች እና መርሖች አንዱ ግልጽነት በመሆኑ በውድድሩ የተሳተፉ ግለሰቦች እና ተቋማት፣ እንዲሁም የቀረቡት የኪነጥበብ ሥራዎች በሙሉ በኢሰመኮ ድረገጽ እና ማኅበራዊ ትስስር/ ገጾች እንዲሁም በተለያዩ አመቺ መንገዶች የሚገለጹ ይሆናሉ።
የዓመታዊው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ዋነኛ ዓላማ የኪነጥበብን እና የሰብአዊ መብቶችን ትስስር ለማጠናከር እና በሁለቱ ዘርፎች መካከል ያለውን ጥምረት በተመለከተ ግንዛቤ ለማስፋፋት፣ እንዲሁም ኪነጥበብ “ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን ማየት” የሚለውን የኢሰመኮ ራዕይ መሳካት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለማስታወስ ነው። በተጨማሪም የፊልም ፌስቲቫሉ የኪነጥበብ ሥራዎችን በውድድር መልክ ሲጋብዝ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን፣ የዚህ ዙር ዓላማ በርካታ ተወዳዳሪዎችን መጋበዝ እና እንዲሳተፉ ማበረታታት ነው። በመሆኑም ለውድድሩ የሚቀርቡ ሥራዎች የቴክኒክ መስፈርቶች ቀለል ያሉ እና በአብዛኛው በተለይም ትኩረት ከተደረገባቸው ከነጻነት መብት እና ከትምህርት መብት ጋር ባላቸው ተያያዥነት የሚገመገሙ ይሆናሉ። ለዚህ ሂደት የኪነጥበብ ሥራዎቹን የቴክኒክ መስፈርት የሚገመግሙ በተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ዘርፎች (በሲቪል እና ፖለቲካ፣ በኢክኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንዲሁም በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞች፣ በአረጋውያን፣ እንዲሁም በስደተኞች፣ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና በፍልሰተኞች መብቶች) የሚሠሩ የኢሰመኮ እና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሙያዎች እንዲሁም የኢሰመኮ የሚድያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራ ክፍል ባለሙያዎችን እና ሌሎች አግባብነት ያላቸው የሥራ ክፍሎች ባለሙያዎች የተካተቱበት፣ ለመጀመሪያ ዙር ግምገማ የ5 ገምጋሚዎች ፓነል፣ ለሁለተኛ ዙር ግምገማ የ7 ገምጋሚዎች ፓነል ይቋቋማሉ። ገምጋሚዎች ከዚህ በታች በተዘረዘሩት የማወዳደሪያ መስፈርቶች ለኪነጥበብ ሥራዎቹ ነጥብ የሚሰጡ ሲሆን፣ ሁሉም ገምጋሚዎች የሰጡት ነጥቦች ድምር አማካይ የኪነጥበብ ሥራው የመጨረሻ ውጤት ይሆናል። ሁለት የኪነጥበብ ሥራዎች ተመሳሳይ ውጤት በሚያገኙበት ጊዜ በገምጋሚ ፓነሉ አብላጫ ድምጽ የሚወሰን ይሆናል። የገምጋሚ ፓነሉ ውሳኔ የመጨረሻ ነው።
በሚከተሉት የማኅበረሰብ ክፍሎች (ልዩ ትኩረት የሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎች) ላይ የሚያተኩሩ የኪነጥበብ ሥራዎች ለውድድሩ መስፈርቶች ከሚሰጡ ነጥቦች በተጨማሪ የማበረታቻ ነጥቦች (Bonus) ያገኛሉ፦ – በሕፃናት እና ታዳጊዎች (ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት ያልበለጡ) – በሴቶች – በአረጋውያን – በአካል ጉዳተኞች – በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወይም በስደተኞች በሁሉም የውድድር ዘፎች ማንኛውም ሰው፣ ማናቸውም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን ድርጅት፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን ወይም የስልጠናና ትምህርት ሰጪ ተቋማት ወይም በተዘረዘሩት ተቋማት የሚሠሩ፣ የሚሰለጥኑ፣ የሚማሩ እና የሚያስተምሩ ግለሰቦች እራሳቸውን ወክለው/በግል መሳተፍ ይችላሉ። በውድድሩ ለመሳተፍ ኢትዮጵያዊ መሆን ያስፈልጋል። ውድድሩ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን እና ተቋማትን ለማበረታታት እና ዐቅም ለመገንባት ያለመ እንደመሆኑ በሀገር ውስጥ የተመዘገቡ ቢሆኑም አልያም ተቀማጭነታቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉ ቢሆኑም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ለሆኑ የሲቪክ ማኅበረሰብም ሆኑ ሌሎች ተቋማት ክፍት አይደለም። በውድድር ለመሳተፍ ምንም ዐይነት ክፍያ አይጠየቅም። የኢሰመኮ ሠራተኞች በሁሉም የውድድር ዘርፎች መሳተፍ የሚችሉ ሲሆን፣ የጥበብ ሥራዎቹ ለዕይታ ለመቅረብ ብቁ ሆነው ከተገኙ ሊመረጡ ይችላሉ። ሆኖም በውድድሩ ለሽልማት እጩ ከሚሆኑ የጥበብ ሥራዎች መካከል አይካተቱም። በአንድ የውድድር ዘርፍ የኪነጥበብ ሥራውን ያቀረበ ተሳታፊ በሌላ ዘርፍ ተጨማሪ የጥበብ ሥራ ለውድድር ማቅረብ ይችላል። ነገር ግን ተሳታፊዎች በአንድ የውድድር ዘርፍ ከአንድ በላይ የጥበብ ሥራ ለውድድር ማቅረብ አይችሉም። ተሳታፊዎች ለሌሎች ውድድሮች ያቀረቧቸውን የኪነጥበብ ሥራዎች ለዚህ ውድድር ማቅረብ ይችላሉ። ሆኖም ተሳታፊዎች ለዚህ ውድድር የሚያቀርቧቸውን የኪነጥበብ ሥራዎች ለውድድሩ አዘጋጆች ከላኩ በኋላ በመገናኛ ብዙኃን አልያም በማንኛውም ማኅበራዊ ሚድያ ሊያሰራጩት አይገባም። የውድድሩ አዘጋጆች ተጨማሪ ማብራሪያ ወይም መረጃ አልያም ከውድድሩ ጋር በተያያዘ ሌላ ምክንያት ተሳታፊዎች በተሳትፎ ቅጹ ባስቀመጡት አድራሻ ለማግኘት ሞክረው፣ ተሳታፊዎች በተገለጸው አድራሻ በተገቢው ጊዜ በማይገኙበት ወይም ምላሽ በማይሰጡበት ወቅት የውድድሩ አዘጋጆች ለውድድር የቀረበውን ሥራ ከውድድሩ ውጪ ሊያደርጉ ይችላሉ። ይህም የኢሰመኮ ውሳኔ የመጨረሻ ነው። ተሳታፊዎች ከሚወክሉት ተቋም ወይም ከእራሳቸው ውጪ ያሉ (የሦስተኛ ወገንን) የኪነጥበብ ሥራዎችን ለውድድሩ ማቅረብ አይችሉም። የኢሰመኮ ይህንን የማረጋገጥ ሙሉ መብት የተጠበቀ ነው። በአንድ የውድድር ዘርፍ በብዛት እና በብቁነት በቂ ተወዳዳሪ አለመኖሩ ከድምዳሜ ላይ ከተደረሰ፣ የውድድሩ አዘጋጆች የውድድር ዘርፉን ሊሰርዙ ይችላሉ። ይህም ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል። ሆኖም ኢሰመኮ በተሰረዘው የውድድር ዘርፍ የተላኩ የኪነጥበብ ሥራዎችን ለተሳታፊዎች የመመለስ ግዴታ ያለበት ሲሆን፣ በተሳትፎ መመሪያ እና ደንቦች አንቀጽ (2) እና (8) መሠረት ጥቅም ላይ ማዋል አይችልም።
ይህ የውድድር ዘርፍ የትምህርት መብት ላይ የሚያተኩር ሲሆን ተሳታፊዎች ትምህርት የማግኘት ወይም የመማር መብትን አስመልክቶ የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ፣ ሐሳብ የሚሰጡ፣ የመብቱ መከበር ወይም መጣስ በተጨባጭ ምን እንደሚመስል የሚገልጹ እና ለማሰላሰል የሚጋብዙ ምስሎችን (ፎቶግራፎችን) የሚያቀርቡበት ነው። የትምህርት መብት ማለት ምን ማለት ነው? የትምህርት መብት የተነፈገ ሰው ሁኔታ ምን ይመስላል? ትምህርት የማግኘት መብት ለሴቶች እና ለወንዶች እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች አንድ ዐይነት ትርጉም አለው? ይህ የፎቶግራፍ ውድድር ዘርፍ እነዚህን እና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በምስል ለመግለጽ እና ለማሰላሰል የሚጋብዝ ነው። በዚህ የውድድር ዘርፍ በጀማሪም ይሁን ልምድ ባለው ባለሙያ ለሚቀርቡ የኪነጥበብ ሥራዎች የመወዳደሪያ መስፈርቶች ተመሳሳይ ናቸው። የፎቶግራፍ ውድድር የቴክኒክ መስፈርቶች – ለውድድር የሚቀርበው ፎቶግራፍ ለዘርፉ ከተመደበው ጭብጥ/ርዕሰ ጉዳይ (ከትምህርት መብት) ጋር ተያያዥነት ያለው ሊሆን ይገባል። – በዚህ ዘርፍ የሚቀርቡ የፎቶግራፍ ሥራዎች ከመስከረም ወር 2017 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ የተነሱ/የተወሰዱ ሊሆን ይገባል። – ለዚህ ውድድር የሚቀርቡ ሥራዎች ከ1 ሜጋ ባይት ያላነሱ እና ከ5 ሜጋ ባይት የማይበልጡ ሊሆን ይገባል። በ JPEG ሴቭ የተደረጉ እና በተቻለ መጠን ለኅትመት አመቺ በሆነ ከፍተኛ የጥራት (ሪዞሉሽን) ደረጃ ሊሆኑ ይገባል። – ለፎቶግራፍ ሥራ ከሚያስፈልገው የአርትዖት (Editing) ሥራ በተጨማሪ፣ መጠነኛ በሆነ መልኩ ፎቶግራፉን ለማሳመር የሚደረጉ (Digital Manipulations) ሥራዎች ተቀባይነት አላቸው። ሆኖም እነኚህ ለውጦች ምን እንደሆኑ እና ለምን ዓላማ እንደተሠሩ በተሳትፎ ቅጹ ላይ በግልጽ ሊመላከት ይገባል። የውድድሩ አዘጋጆች ይህንን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለተሳታፊው ሊያቀርቡ ይችላሉ። እንዲሁም ተጨማሪ ሥራዎች ያልተሠራበትን (ኦሪጂናል) ፎቶግራፍ እንዲላክ ሊጠይቁ ይችላሉ። – ተሳታፊው የሚጠቀመው ካሜራ ቢያንስ 3000 ፒክሰል (ወደ ጎን) እና 300 DPI/PPI Setting ሊሆን ይገባል። በሞባይል/ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚነሱ ፎቶግራፎች ይህንን መስፈርት ማሟላት የሚጠበቅባቸው ባይሆንም፣ ለውድድር ተቀባይነት የሚኖራቸው ከፍተኛ ጥራት (High Resolution) ያላቸው እና ከተመደበው ጭብጥ/ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ከሆነ ብቻ ነው። – በተለይ በአንድ ሰው ላይ የሚያተኩሩ ፎቶግራፎች ከሆኑ የዛን ሰው ሙሉ ፈቃድ ማግኘት፣ ከ18 ዓመት በታች የሆነ ታዳጊ ላይ የሚያተኩር ከሆነ ደግሞ በሕግ ሙሉ መብት ያለውን ወይም የአሳዳጊ ሙሉ ፈቃድ ማግኘቶትን ያረጋግጡ። – Collage ወይም በአንድ ፍሬም በርካታ ምስሎችን የያዘ ፎቶግራፍ በውድድሩ አይካተትም። ለውድድር በሚቀርበው ፎቶግራፍ ላይ ፊርማ፣ Watermark፣ Overlay እና የመሳሰሉትን ምልክቶች ወይም ጽሑፎች መጨመር አይገባም። – በሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) የተዘጋጁ ፎቶግራፎች ተቀባይነት የላቸውም፤ ከውድድሩ ውጭ ይደረጋሉ፡፡
ይህ የውድድር ዘርፍ በነጻነት መብት ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ተሳታፊዎች በነጻነት መብት ትርጉም፣ የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ፣ ሐሳብ የሚሰጡ፣ የመብቱ መከበር ወይም መጣስ በተጨባጭ ምን እንደሚመስል የሚገልጹ እና ለማሰላሰል የሚጋብዙ አጫጭር ቪድዮዎችን የሚያቀርቡበት ነው። በዚህ የውድድር ዘርፍ ተሳታፊዎች በአንድ ሰው ዙሪያ (የራሳቸው አልያም የሦስተኛ ወገን) ቢያተኩሩ የሚመረጥ ቢሆንም፣ ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር የተያያዙ የኪነጥበብ ሥራዎችን ማቅረብ ይችላል። አልያም በሕይወት ዘመናቸው በተለያዩ ዘርፎች አስተዋጽዖ ባደረጉ ሰዎች ዙርያ የሚያተኩር ሊሆን ይችላል። የነጻነት ዋጋ ምን ያክል ነው? ትርጉም ያለው ነጻነት ምን ማለት ነው? ነጻነት ለሴቶች፣ ለሕፃናት፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአረጋውያን፤ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ እና ለስደተኞች እኩል ዋጋ አለው? ወዘተ. . . ርዕሰ ጉዳዩ ሰፊ እንደመሆኑ መጠን ይህ የአጫጭር ፊልሞች ውድድር ዘርፍ እነዚህን ወይም ሌሎች የነጻነት መብትን ለማሰብ እና ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎችን ለማስታወስ የሚጋብዝ ነው። በዚህ ውድድር መመሪያ እና ደንቦች በተገለጸው መሠረት ማስታወቂያ የሚያካትቱ የኪነጥበብ ሥራዎች ከውድድሩ ውጪ ይደረጋሉ። በዚህ የውድድር ዘርፍ ልብ ወለድ አልያም የዘገባ ሥራዎች (Narrative or Documentary) ማቅረብ የሚቻል ቢሆንም፣ የሙዚቃ እና የዳንስ ይዘት ያላቸው ሥራዎች በዚህ ውድድር አይካተቱም። በሂደት ላይ ያሉ ወይም ያልተጠናቀቁ የኪነጥበብ ሥራዎችም ተቀባይነት አይኖራቸውም። በዚህ ዘርፍ በጀማሪ ባለሙያም ይሁን ልምድ ባለው ባለሙያ የተዘጋጁ ለውድድር የሚቀርቡ አጫጭር ፊልሞች እንዲሁም በሞባይል/ተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም በካሜራ አማካኝነት ለተሠሩ የኪነጥበብ ሥራዎች የመወዳደሪያ መስፈርቶች ልዩነት የላቸውም። የአጫጭር ፊልሞች ውድድር የቴክኒክ መስፈርቶች – ለውድድር ዘርፉ ከተመደበው ጭብጥ/ርዕሰ ጉዳይ (ከነጻነት መብት) ጋር የተያያዘ መሆን አለበት። – በአጠቃላይ በጀማሪ ዘርፍ ከ5 ደቂቃዎች ያላነሰ እና ከ6 ደቂቃዎች ያልበለጠ ርዝመት እንዲሁም በባለሙያዎች ዘርፍ ከ10 ደቂቃዎች ያላነሰ እና ከ15 ደቂቃዎች ያልበለጠ ርዝመት። – በዚህ ዘርፍ የሚቀርቡ ሥራዎች ከመስከረም ወር 2017 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ የተነሱ/የተቀረጹ ሊሆኑ ይገባል። – በእንግሊዘኛ ቋንቋ ወይም በማንኛውም የኢትዮጵያ ቋንቋ የተሠራ ሥራ ለውድድሩ መቅረብ ይችላል። ሆኖም በአማርኛ ወይም በእንግሊዘኛ ቋንቋ “ሰብታይትል” ሊደረግ ይገባል። – በተንቀሳቃሽ ስልክ ለሚቀረጹ አጫጭር ፊልሞች ለማሰራጨት በአብዛኛው ተመራጩ መንገድ ዩትዩብ እንደመሆኑ፣ ለዚህ ውድድር ዘርፍ የሚያገለግሉ የቴክኒክ መስፈርቶች የዩትዩብ መድረክ የሚጠይቃቸው ናቸው። በዋነኛነት ለውድድር የሚቀርቡ ሥራዎች የሚከተሉትን የጥራት መስፈርቶች ሊያሟሉ ይገባል። Aspect ratio: 9:16 (Creates the Vertical Format) Resolution: 1920 pixels by 1080 pixels (Standard Length by Width Ratio for Vertical Content) ለዚህ ዘርፍ ለውድድር የሚቀርቡ ሥራዎች ማናቸውም የቪድዮ ዐይነቶች ሊሆኑ ይችላሉ፦ Animated፣ Live-action፣ Screen recording፣ Whiteboard፣ Motion graphics፣ Typography ወይም Combination። – ለውድድር የሚቀርቡ አጫጭር ፊልሞች በሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) የተዘጋጁ ሊሆኑ አይገባም፡፡ ነገር ግን የመወዳደሪያ ሥራቸውን በAnimation ማቅረብ የሚፈልጉ ተወዳዳሪዎች በተወሰነ መልኩ ሊጠቀሙት ይችላሉ፡፡ ሆኖም የውድድር ሥራው ሙሉ በሙሉ ወይም በአብዛኛው በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተዘጋጀ ከሆነ ከውድድር ውጪ ይደረጋል፡፡ – ተመራጭ Formats: An H264 or MP4 file compressed from the original 1080p or 720P master. ቢያንስ ሊያሟላ የሚገባው መስፈርት (Minimum Acceptable): An H264 or MP4 file at 480i. Do not rip from a DVD unless you have no other option. – ለውድድር በሚቀርበው የኪነጥበብ ሥራ ላይ ፊርማ፣ Watermark፣ Overlay እና የመሳሰሉትን ምልክቶች ወይም ጽሑፎች መጨመር አይገባም። – የምስጋና/ የዕውቅና ፍሬሙ ከ1 ደቂቃ ሊበልጥ አይገባም። – በሞባይል አጫጭር ፊልሞችን ስለመቅረጽ ጠቃሚ ማብራሪያ እዚህ ወይም እዚህ ማግኘት ይቻላል። እንዲሁም አጫጭር ፊልሞችን ስለመቅረጽ ጠቃሚ ማብራሪያ እዚህ ያገኛሉ። – ኢሰመኮ ለሦስተኛ ወገን ይዘቶች ኃላፊነት አይወስድም።
ከመስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2018 ዓ.ም. (እኩለ ለሊት ወይም በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከለሊቱ 6፡00 ሰዓት) ድረስ ለውድድር የሚቀርበውን የጥበብ ሥራ እንዲሁም የተሞላ እና የተፈረመበት የተሳትፎ ቅጽ በማያያዝ ከዚህ በታች በተመለከተው አድራሻ መላክ ይችላሉ።
ከዚህ በላይ በተገለጹት የኢሰመኮ ጽሕፈት ቤቶች በአካል ተገኝተው የኪነጥበብ ሥራቸውን ለሚያቀርቡ ተሳታፊዎች የሚሞላው የተሳትፎ ቅጽ እና ፖስታ ይዘጋጃል።
በኢሰመኮ ድረገጽ አልያም በማኅበራዊ ሚዲያ አድራሻዎች አስተያየት መስጫ በኩል አልያም በሌላ መንገድ የሚላኩ የኪነጥበብ ሥራዎች በውድድሩ አይካተቱም ወይም ከውድድሩ ውጪ ይሆናሉ። የተሟላ የተሳትፎ ቅጽ ያላያያዙ የኪነጥበብ ሥራዎች ወይም መረጃ በተሟላ መልኩ ያላቀረቡ የኪነጥበብ ሥራዎች በውድድሩ አይካተቱም ወይም ከውድድሩ ውጪ ይሆናሉ። በሲዲው (CD) ወይም በፍላሽ ዲስኩ (USB) ለውድድር ከሚቀርበው የኪነጥበብ ሥራ ውጪ ሌላ ምንም ዐይነት ይዘት ሊኖር አይገባም። ግልጽ ያልሆነ፣ የማይነበብ ወይም ሌሎች የቴክኒክ ግድፈቶች ያሉበት ፋይል አልያም ከሌሎች ይዘቶች ጋር የሚላኩ የጥበብ ሥራዎች ከውድድር ውጪ የሚደረጉ ሲሆን፣ ለዚህም የኢሰመኮ ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል።
This site was created with the Nicepage